Search

የአሜሪካ ኩባንያዎችን ቀልብ የሳበው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ

ረቡዕ ሚያዝያ 14, 2018 183

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የላቀ ተወዳዳሪ የሚያደርጋትና የሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ስኬትን የሚያበስረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (Mega Airport) ግንባታን፣ መንግሥት በራሱ አቅም እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር መግባቱ ይታወሳል።

10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቀው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ልማት ባንክ በኩል የብድር ፍላጎቷን ስታቀርብ የቆየች ቢሆንም፣ እስካሁን ከተገኘው 500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ውጭ ሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለብድር ጥያቄው ፈጣን ምላሽ አልሰጡም።

ይሁን እንጂ መንግሥት የውጭ ብድርን ብቻ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ለአሥር ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የቆየውንና ውጤታማነቱ የተረጋገጠውን ይህን ታላቅ ፕሮጀክት በራሱ አቅም ግንባታውን ጀምሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፕሮጀክቱ ስልታዊ ጠቀሜታና ተስፋ ሰጭነት የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል። ሰሞኑን በአሜሪካ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የፋይናንስ ሮድሾው (Finance Roadshow) መድረክ ላይ፣ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ እንደገለጸው፣ የአሜሪካ ኩባንያዎች በምህንድስና፣ በቴክኖሎጂ፣ በደህንነትና በአሠራር ዘርፎች ያላቸውን የላቀ ብቃት በመጠቀም በፕሮጀክቱ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ደጋግመው እንደገለጹት፣ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የአቪዬሽን ተወዳዳሪነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው።

የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባት የኢትዮጵያን የንግድና የቱሪዝም ፍሰት ከማሳደጉም በላይ፣ ሀገራችን የዓለም የአቪዬሽን ማዕከል እንድትሆን ያስችላታል።

የመንግሥት የራስን አቅም የመጠቀም ውሳኔ እና የአሜሪካ ኩባንያዎች ያሳዩት ከፍተኛ ፍላጎት ተደምሮ፣ ፕሮጀክቱ የአሜሪካን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የልማት ራዕይ ጋር የሚያስተሳስር እውነተኛ የንግድ አጋርነት መፍጠር እንደሚያስችል ተመላክቷል።

ይህ ትብብር እውን ከሆነ ለሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ብልጽግና ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ማዕከል የማስፋፋት ግብም በታቀደለት ጊዜ ስኬታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር፣ ኢትዮጵያ ለታላላቅ ፕሮጀክቶች ያላትን ቁርጠኝነትና በራስ የመቆም አቅሟን የምታሳይበት አዲስ የብስራት ዜና ሆኖ ለአፍሪካ ተምሳሌትነቷን ያረጋግጣል።

በላሉ ኢታላ