Search

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ አገኘ

ረቡዕ ሚያዝያ 14, 2018 63

በዋሽንግተን በተካሄደ ከፍተኛ የፋይናንስ ማስተዋወቅ መድረክ፣ የአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት፣ ታዋቂ የፋይናንስ ድርጅቶችና ታላላቅ የዘርፉ ተዋናዮች ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ያላቸውን ድጋፍ ገለጹ። 

ይህም አፍሪካ ካሏት ግዙፍ የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውን ይህን ግንባታ ወደ ተግባር ለመቀየር ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ግልጽና በግል ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካን ትስስር የሚቀይር፣ የንግድ ፍሰትን የሚያሳልጥና ኢትዮጵያን ቀዳሚ የዓለም አቀፍ አቪዬሽንና ሎጂስቲክስ ማዕከል የሚያደርግ መሆኑም በውይይቱ ወቅት ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ንግድን፣ ኢንቨስትመንትንና ትስስርን ለመክፈት ታስቦ የተዘጋጀ ቅድሚያ የሚሰጠው ፕሮጀክት ነው ብለዋል። 

በዋሽንግተን የታየው ጠንካራ ተሳትፎ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ያለውን መተማመን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ ከአሜሪካ አጋሮች ጋር ያለው ትብብር ለአየር መንገዱ ዓለም አቀፋዊ ስኬት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ እየጨመረ የመጣውን የተሳፋሪና የጭነት ፍላጎት ለማሟላት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሳቱ ንሴሌ፣ ፕሮጀክቱ አዋጭና ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አረጋግጠዋል።

 “የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጣናዊ ውህደትን የሚያፋጥን፣ ተወዳዳሪነትን የሚጨምርና በአፍሪካ ዘላቂ ዕድገትን የሚያመጣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በዋሽንግተን የተካሄዱት ውይይቶች በፋይናንስ አወቃቀርና በአተገባበር መንገዶች ላይ ተጨባጭ መሻሻሎችን ያሳዩ ሲሆን፣ ግንባታውን ወደ ተግባር ለማስገባት የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያፋጥኑም የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

በሀይማኖት ከበደ

#EBC #Ethiopia #USA #Aviation #BishoftuAirport #Infrastructure #EthiopianAirlines #StrategicPartnership