Search

ኢትዮጵያን ቀዳሚ የአፍሪካ አቪየሽን ማዕከል የሚያደርገት የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ

ዓርብ ሚያዝያ 16, 2018 85

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አቪዬሽን ዘርፍ ያለውን ቀዳሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር፣ አህጉሪቱን ከቀሪው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ማዕከል መገንባት ጀምሯል።

በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገነባው ይህ አዲስ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቁልፍ የመጓጓዣ ማዕከል የሚያደርጋት እና የዓለም አቀፉን የአቪዬሽን ታሪክ የሚቀይር ታላቅ ፕሮጀክት ነው። 

ግዙፍ የመስተንግዶ አቅም 

የአውሮፕላን ማረፊያው የመጀመሪያ ዙር ግንባታ እ.ኤ.አ በ2030 ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 110 ሚሊዮን መንገደኞች ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህም በአሁኑ ወቅት በዓለም ቀዳሚ ከሆነው የአሜሪካው አትላንታ አውሮፕላን ማረፊያ በላቀ ደረጃ ግዙፍ ያደርገዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መሥፍን ጣሰው ለሲኤንኤን እንደገለጹት፤ ይህ አውሮፕላን ማረፊያ ዱባይና ዶሃ ለመካከለኛው ምሥራቅ ያላቸውን ዓይነት ስልታዊ ሚና ለአፍሪካ እንዲኖረው ታስቦ የተወጠነ ነው።

የአህጉራዊ ትስስር ሚና 

ይህ ግዙፍ ማዕከል የአፍሪካውያንን የትራንስፖርት ትስስር በእጅጉ እንደሚቀይረው ይጠበቃል። ቀደም ሲል ከአንድ የአፍሪካ ከተማ ወደ ሌላው ለመጓዝ አውሮፓ መድረስ ይገደዱ ለነበሩ መንገደኞች፣ አዲሱ ማዕከል በገዛ አህጉራቸው በቀላሉ እና በፍጥነት እንዲገናኙ መንገድ ይከፍታል። ይህም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ስምምነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

የጭነት ትራንስፖርት እና የምጣኔ ሀብት ዕድገት 

የአፍሪካ የአየር ጭነት ፍላጎት በየዓመቱ ከ15 እስከ 16 በመቶ እያደገ ሲሆን፣ ይህም ከዓለም አማካይ ዕድገት በሦስት እጥፍ ይበልጣል። አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት 3.73 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የሚኖረው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ሎጂስቲክስ ማዕከል ያደርጋታል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት ቁልፍ ጉዳዮች 

በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ላንድሪ ሲኜ እንዳብራሩት፣ የፕሮጀክቱ ስኬት ከአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ባለፈ ከሌሎች መሠረተ ልማቶች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። እንደ ዘመናዊ የባቡር እና የመንገድ ትስስር፣ ቀልጣፋ የጉምሩክ አሠራር እንዲሁም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ያሉ ጉዳዮች ለአየር ማረፊያው ውጤታማነት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

የስምጥ ሸለቆን ተፈጥሯዊ ውበት ከዘመናዊ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ ጋር አጣምሮ የያዘው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ እና አካባቢን የሚጠብቅ አረንጓዴ ፕሮጀክት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ግዙፍ ኢንቨስትመንት የዓለም አቀፍ አቪዬሽን አዲሷ ማዕከል ለመሆን የምታደርገው ጉዞ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀይረው ይጠበቃል። 

በላሉ ኢታላ