ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ በምትገነባው ኢኮኖሚ ልክ የሆነ የባሕር በር ማግኘት አለባት" ሲሉ የገለጹት ሐሳብ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በሳይንሳዊ መረጃዎችና በሀገራችን የረጅም ጊዜ ህልውና ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂካዊ ጥያቄ መሆኑን ተጨባጭ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከምሥራቅ አፍሪካም አልፎ ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለችና በሕዝብ ቁጥርም ከአፍሪካ ሁለተኛ እንዲሁም ከዓለም ቀዳሚዎቹ 12 ሀገራት አንዷ የሆነች ግዙፍ ሀገር ናች። ይሁንና ይህ እውነታ ቢኖርም፣ የሀገራችን የወጪና ገቢ ንግድ በአንድ ጠባብ የባሕር በር ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ይገኛል።
የኢኮኖሚው ግስጋሴ እና የጥሬ ዕቃ ፍላጎት
ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ይገኛል። የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሀገራችንን ዕድገት በተመለከተ 9.2 በመቶ የሆነ አዎንታዊ ግምቶችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ በመንግሥት ይፋዊ ዕቅድ መሠረት ደግሞ በዚህ ዓመት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን ተከትሎ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እየመጣ ያለው አበረታች ለውጥ ኢትዮጵያ ትክክለኛ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ያሳያል። ሆኖም የአምራች ዘርፉ ማነቆ የሆነው የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና የወጪ ንግድ ስትራቴጂ በአሁኑ ወቅት የተጨማሪ ባሕር በር አስፈላጊነትን ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ አድርጎታል።
በግብርናው ዘርፍም ባለፈው ዓመት 836.9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት 892.2 ሚሊዮን ኩንታል ይደረሳል ተብሎ ታቅዷል። ይህን የመሰለ ግዙፍ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብና ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማስገባት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ካለው አንድ የባሕር በር አማራጭ በላይ ይፈልጋል።
የሕዝብ ቁጥር ጫና እና የወደፊት ተስፋ
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት። ይህን የሕዝብ ቁጥር እና እየተፋጠነ ያለውን ልማት ሊሸከም የሚችል የባሕር በር ማግኘት ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ ነው። በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮን አዳዲስ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ወደ ገበያ የሚቀላቀሉ ሲሆን፣ እነዚህን ዜጎች በሥራ ለማሰማራት የሀገራችን የንግድ እንቅስቃሴ በዓመት በሁለት አኃዝ ማደግ ይኖርበታል።
ይሁን እንጂ ባሕር በር አልባ መሆን ንግዱን በማቀዝቀዝ የሥራ ዕድል ፈጠራውን እጅጉን እየገደበው ይገኛል። በአሁኑ ሁኔታ በባሕር በር እጦት የሚፈጠረው የሎጂስቲክስ መስተጓጎል ሳይቆጠር፣ ለወደብ ኪራይ ብቻ ሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ትከፍላለች። በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በባሕር በር ላይ በሚደርሰው እንግልት እና ወጪ ምክንያት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዓመት ከ30 ሺህ ብር በላይ የማይታይ ቀረጥ (Hidden Tax) ከኪሱ ይከፍላል። በዓለም አቀፍ ስምምነቶች በሚገኝ የማለፊያ መብት (Right of Transit) ብቻ ያውም በራሷ በማትቆጣጠረው አንድ በር መወሰኗ፣ የዜጎቿን የብልጽግና ጉዞ በሌሎች ፈቃድ ስር እንዲወድቅ አድርጎታል።
የባሕር በር እጦት የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ኪሳራ በዝርዝር
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት (PSI) ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የባሕር በር ባለቤት ባለመሆን የሚባክነው ሀብት እጅግ ከፍተኛ ነው። ሀገራችን በየዓመቱ ከ19 ቢሊዮን እስከ 31 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) ታጣለች። ይህም ማለት ከአጠቃላይ ምርቷ ውስጥ እስከ 23 በመቶ የሚሆነው በወደብ እጦት ምክንያት ይባክናል ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ለባሕር በር አገልግሎት ክፍያ ብቻ በየዓመቱ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣ ሲሆን፣ በሎጂስቲክስ መጓተት ምክንያት የአንድ ምርት ዋጋ በ15.2 በመቶ እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ የዋጋ ጭማሪ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በመስተጓጎል የሚደርሰውን የዋጋ ጭማሪ በንጽጽር ብናይ አልባሳትን ወደ ጀርመን ለመላክ የሚጠየቀው የትራንስፖርት ወጪ ከቬትናም ጋር ሲነጻጸር በ247 በመቶ፣ ከባንግላዴሽ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ72 በመቶ በልጦ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን አምራቾች ምርታቸውን ለዓለም ለማቅረብ ከሌሎች ሀገራት እጅግ የላቀ ወጪ ለመክፈል እንደሚገደዱ ነው።
ከሎጂስቲክስ ባለፈ፡ "የመተላለፊያ መሿለኪያ" (Tunnel Effect) ስጋት
ለኢትዮጵያ የባሕር በር አስፈላጊነት ከወጪ ንግድ ባለፈ ሀገራዊ የልማት ስርጭትን የሚወስን ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅት የሀገራችን 95 በመቶ ንግድ በአንድ መስመር ብቻ የሚከናወን በመሆኑ፣ ልማቱ በዚያው ኮሪደር ላይ ብቻ እንዲከማች አድርጓል። ይህ የመተላለፊያ መሿለኪያ (Tunnel Effect) ተብሎ የሚጠራው ክስተት አዲስ አበባና በወደቡ መስመር ላይ ባሉ ከተሞች ላይ ብቻ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ክምችት እንዲፈጠር ሲያደርግ፣ ሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ግን ለባሕር በር ቅርብ ባለመሆናቸው ልማቱ በበቂ ሁኔታ ሳይደርሳቸው እንዲቆዩ አድርጓል። የባሕር በር አማራጮችን ማስፋት ማለት የልማት አድማሱን ወደ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ የሀገራችን ክፍሎች በእኩልነት ማዳረስ ማለት ነው።
ስትራቴጂካዊ አማራጮችና የቀጣናዊ ሁኔታ
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የባሕር በር ጥገኝነት ለመቀነስ የጀመረቻቸው የላሙ (LAPSSET) ኮሪደር ግንባታ እና ሌሎች አማራጭ ወደቦችን መፈለግ መጀመሯ ትክክለኛ የስትራቴጂካዊ ነፃነት እርምጃዎች ናቸው። 25 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው የላሙ ኮሪደር፣ ለደቡብና ለምዕራብ ኢትዮጵያ አዲስ የኢኮኖሚ በር ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በምትገነባው የኢኮኖሚ ግዙፍነት ልክ የባሕር በር እንዲኖራት መጠየቋ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎት፣ የዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ግፊት እና በቢሊዮን የሚቆጠር የዶላር ኪሳራን ለማስቀረት የራሷ የሆነ ቋሚና አስተማማኝ የባሕር መዳረሻ ማግኘቷ የግድ ይላል። ይህ ፍላጎት በቀጣናው ሀገራት መካከል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚፈጸም መሆኑ ደግሞ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትስስርና ዘላቂ ሰላም ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት ሳይሆን፣ በቁጥር የሚገለጽና በዜጎች የቀን ተቀን ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ የኢኮኖሚ ነፃነት ጥያቄ ነው የምንለውም ለዚህ ነው።
በለሚ ታደሰ