ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበችው ያለው 9.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ሀገሪቱ ካለፉት ስምንት ዓመታት የ7.5 በመቶ አማካይ ዕድገት ተነስታ ወደ አዲስ የምርት ምዕራፍ መሸጋገሯን የሚያበስር ታላቅ ክስተት ነው፡፡
ይኽ እድገት በመጪው ዓመት ወደ10.2 በመቶ እንደሚያድግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ይህ ስኬት ከቁጥር ባለፈ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ እየታየ ያለውን ሥር-ነቀል ለውጥ የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይም የኢንዱስትሪው ዘርፍ በ13.2 በመቶ ዕድገት ግንባር ቀደሙን የዕድገት ሞተርነት ሚና ተረክቧል፡፡
ኢትዮጵያ የገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ዞኖችና ፓርኮች ዛሬ የሀገሪቱ የማምረት አቅም ቁልፍ መገለጫ ሆነዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ የወጪ ምርት ዙሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች 175,237,561.04 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዶ ኤክስፖርት የተደረገው 187,227,414.77 የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ምርት ሲሆን በዚህም የዕቅዱን 100+% መፈጸም እንደተቻለ ያሳያል። የዘጠኝ ወራት የኤክስፖርት አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ103,991,534.56 የአሜሪካን ዶላር ወይንም በ100+% ጨምሯል፡፡ በፓርኮች ውስጥ ያሉት ሼዶች የመያዝ ምጣኔ (Occupancy Rate) 89 በመቶ መድረሱ፣ ዘርፉ ለውጭና ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ያለውን ከፍተኛ ማራኪነት ያረጋግጣል።
እንደ ሀዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ ቂሊንጦ እና ድሬዳዋ ያሉ የኢንዱስትሪ ማዕከላት ከ70,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 17,000 የሚሆኑት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ዞኖች የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚካሄድባቸው እና የሀገር ውስጥ አምራቾች ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የሚተዋወቁባቸው የዕውቀት ማዕከላት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
"ኢትዮጵያ ታምርት" እና የተኪ ምርት ስኬት
"ኢትዮጵያ ታምርት" የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ፣ የኢንዱስትሪ ዞኖችንና ማዕከላትን በማነቃቃት ረገድ ታላቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 4.85 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን መታደግ ተችሏል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከውጭ ጥገኝነት ወጥታ ወደ ኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
በዚህ ንቅናቄ አማካኝነት 830 ሥራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ምርት የተመለሱ ሲሆን፣ 325 አዳዲስ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችም ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ46 በመቶ ወደ 66.3 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያ የምትከተለው የኮሪደር እና የኢንዱስትሪ ማዕከላት ልማት፣ በዓለም ላይ ስኬታማ ከሆኑት እንደ ቬትናም እና ቻይና ተሞክሮ ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ ቬትናም በ20 ዓመታት ውስጥ ያስመዘገበችው እምርታዊ ዕድገት መሠረቱ የኢንዱስትሪ ክላስተሮችን እና የልማት ቀጠናዎችን በስትራቴጂ መምራቷ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ መንገድ በመከተል፣ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን ከፖሊሲ ማሻሻያዎች ጋር በማጣመር የ"አፍሪካ አንበሳ" (African Lion) ተምሳሌትነቷን እያረጋገጠች ነው፡፡
በአጠቃላይ በሦስተኛው ሩብ ዓመት የታየው የኢንዱስትሪ ግስጋሴ፣ የልማት ኮሪደሮች እና የኢንዱስትሪ ዞኖች ቅንጅታዊ ትስስር ውጤት ነው፡፡ እነዚህ አውታሮች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር በማዘመን፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የኤክስፖርት አቅምን በማሳደግ ለብሔራዊ ብልጽግና ጽኑ መሠረት እየጣሉ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም "ኢትዮጵያ ታምርት" የሚለውን መርህ ይበልጥ በማጠናከር እና የኮሪደር ልማቱን ስኬቶች ወደ ሁሉም ክልሎች በማስፋፋት፣ የሀገራችንን የኢንዱስትሪ ህዳሴ ዳር ማድረስ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ታምርት!
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ