የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ "አካታች የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ንቅናቄ አስጀምሯል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪያ መርሆችን መሠረት ያደረጉ የባንክ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማስፋትና ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል።
ባንኩ አጠቃላይ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች የባንክ አገልግሎትን ለሁሉም ለማዳረስ ይህንን ሀገራዊ ንቅናቄ በይፋ የጀመረ ሲሆን፣ ይህም የብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል የፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

ይህ ይፋ የተደረገው መጠነ-ሰፊ የንቅናቄ ፕሮግራም ከግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት ወር 2019 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ በሂደቱም በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ 241 ወረዳዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በእነዚህ ወረዳዎች ውስጥ በሚደረጉ የተቀናጁ እንቅስቃሴዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ተገልጋዮችን ወደ ፋይናንስ ሥርዓቱ ለማስገባትና ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አስታውቀዋል።
አካታች የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ለአጠቃላይ የሀገር ልማትና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ የተያዘው ታላቅ ዕቅድ በተግባር ተተርጉሞ ስኬታማ እንዲሆን የእምነቱ አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ጥረትና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።