Search

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለበጀት ጉድለት የሚወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ ቆሟል - የገንዘብ ሚኒስቴር

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 81

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት 2019 የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለበጀት ጉድለት ከብሔራዊ ባንክ ምንም ዓይነት ብድር እንዳልወሰደ ገልጸዋል።

ይህም የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር በእጅጉ እንደረዳ እና ወደ ነጠላ አኃዝ እንዲወርድ እንዳገዘ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ ካሉ የዓለም ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው። 2012 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት 6.8 በመቶ 2017 ደግሞ 9.2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በተያዘው ዓመት ደግሞ 10.2 በመቶ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በነሐሴ 2014 . 34.5 በመቶ ደርሶ የነበረው የዋጋ ንረት በመጋቢት 2018 . ወደ 9.4 በመቶ ማውረድ ተችሏል ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።

ለኢኮኖሚው ፈጣን ዕድገት ምርት እና ምርታማነት ማረጋገጥ መቻሉ እና የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ትልቅ ሚና እንደነበራቸውም አብራርተዋል።

ባንኮች ወደ ገበያው የሚለቅቁት የገንዘብ ፍሰት ከኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ መሆኑ እና ውጤታማ የገንዘብ ፖሊሲዎች ትግበራ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ አንዱ ግብአት ነበር ብለዋል።

ወደ ገበያ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ሽግግር የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ከመቅረፉም ባለፈ በሕጋዊ እና በትይይዩ ገበያ መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት እንዲጠብብ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ ዘመናዊ እና ውጤታማ ሥራዎች እንዲሠራ አድርጓል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ