Search

ለማዳበሪያ እና ለነዳጅ ድጎማ ከ236 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዟል - የገንዘብ ሚኒስቴር

ሓሙስ ሰኔ 04, 2018 78

2019 በጀት ዓመት ለማዳበሪያ እና ለነዳጅ ድጎማ 236.4 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2019 በጀት ዓመት መነሻ ዕቅድን ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት፣ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ከአምናው ተመሳሳይ በጀት ጋር ሲነጻጸር 21.3 በመቶ ዕድገት እንዳለው ገልጸዋል።

በበጀቱ የተያዙት ለክልል መንግሥታት፣ ለዕዳ ክፍያ፣ ለልማት ሥራዎች እና ለመሠረታዊ ድጎማዎች ከአምናው ጭማሪ መኖሩን አመልክተዋል።

ለነዳጅ እና ለማዳበሪያ ድጎማ የተያዘው በጀት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ አለው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህም የሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ ነው ብለዋል።

ለመንገድ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 121.8 ቢሊዮን ብር፣ ለትምህርት ዘርፍ ፕሮጀክቶች 61.3 ቢሊዮን ብር፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ 30.5 ቢሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።

ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ለከተማ እና ለገጠር ሴፍትኔት ፕሮግራሞች፣ ለተፈጥሮ እና ለጤና ዘርፎች በጀት መያዛቸውንም አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ