Search

ከ1 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም በአውስትራሊያ ከባድ የህግ ክስ ገጠመው

ሓሙስ ሐምሌ 23, 2018 185

በቀን ለረጅም ሰዓታት ለመልዕክት፣ ለመደዋወያ አለፍ ሲልም ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን ለመጋራት የምንጠቀምበት ቴሌግራም፤ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን የሚያራምዱ ይዘቶችን በበቂ ሁኔታ አላስወገደም በሚል በአውስትራሊያ መንግሥት የሕግ እርምጃ ተጀምሮበታል።

የአውስትራሊያ የበይነመረብ ደህንነት ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ ኩባንያው የሽብር ግድያዎችን እና የጅምላ ተኩስ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ለማስወገድ በቂ እርምጃ አልወሰደም።

 

ኮሚሽነር ጁሊ ኢንማን ግራንት በመግለጫቸው እንዳብራሩት፣ ከተወቀሱት ይዘቶች መካከል የኒውዚላንዱ ክራይስትቸርች እና የአሜሪካው ቡፋሎ አሰቃቂ ጥቃቶች ይገኙበታል።

ቴሌግራም ማሳሰቢያ ከተሰጠው በኋላም እነዚህ ይዘቶች ለረጅም ጊዜ ተደራሽ ሆነው መቀጠላቸውን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።

በፍርድ ቤት ሰነዶች መሠረት፣ ከሐምሌ እስከ ጥቅምት 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ አውስትራሊያውያን 12 የሽብር ይዘት ያላቸውን ፖስቶችን ለቴሌግራም ሪፖርት ያደረጉ ቢሆንም፤ መተግበሪያው 10 የሚሆኑትን ፖስቶች ከማስወገድ ወይም ያጋሩትን አካውንቶች ከመዝጋት ተቆጥቧል።

ፍርድ ቤቱ ቴሌግራም የአውስትራሊያን የዲጂታል ደህንነት ህጎች ጥሷል ብሎ ከወሰነ፣ ኩባንያው እስከ 54.6 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር (ወይም 38 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) የሚደርስ ከባድ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል።

ይሁን እንጂ ቴሌግራም የቀረበበትን ክስ ሙሉ በሙሉ በመቃወም ጉዳዩን በፍርድ ቤት እንደሚከራከር ገልጿል።

የኩባንያው ቃል አቀባይ ቴሌግራም አክራሪነትን ለመዋጋት ጠንካራ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በ2026 ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ አክራሪ ቡድኖችን መዝጋቱን በማስታወስ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዓለም ላይ በወር ከ1 ቢሊዮን በላይ ንቁ ተጠቃሚዎች ያሉት ይህ ግዙፍ ተቋም፣ በቅርቡ በተለያዩ የፖለቲካ ውጥረቶች ውስጥ እያለፈ ይገኛል።

ትውልደ ሩሲያዊው የቴሌግራም መስራች ፓቬል ዱሮቭ በ2014 ሩሲያን ለቆ ከወጣ በኋላ በ2017 ኩባንያውን ወደ ዱባይ ያዛወረ ሲሆን፤ መተግበሪያው በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ወቅት ለሞስኮም ሆነ ለኪየቭ ባለስልጣናት ወሳኝ የመረጃ ልውውጥ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ሆኖም ባለፈው ረቡዕ ሩሲያ መተግበሪያው በዩክሬን ሰላዮች ጥቃት ለማቀነባበር እየዋለ ነው በሚል ፓቬል ዱሮቭን የሽብርተኝነት ተግባርን በማመቻቸት ወንጀል መክሰሷ የዚሁ ውጥረት አካል መሆኑ ተዘግቧል።

በቃልኪዳን መዓድን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: