በትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴን የማነቃቃት እና ገበያን የማረጋጋት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በክልሉ የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የኢኮኖሚና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ የባለአደራ አስተዳደር ከተቋቋመ ጀምሮ የተጎዱ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ መዋቅሮችን በመዘርጋት እና ችግሮች በማቃለል ሕዝቡን ወደ መደበኛ ህይወቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በትግራይ ክልል በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ምክንያት ተቋርጠው የቆዩ መደበኛ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመሠረተ ልማቶች አውታሮች ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በሕገ ወጡ ሕወሓት የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮች መልሶ ለመዘርጋት እና የሕዝብ አገልግሎቶች ለማስቀጠል ጊዜያዊ አስተባባሪዎችን በመመደብ በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ገበያ እንዲነቃቃ እና የምግብና የምግብ ነክ ሸቀጦች እንዲሟሉ ባለአደራ አስተዳደሩ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም የአቅርቦት እጥረቱ እየተቀረፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሕዝብ የንቅናቄና የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ቴዎድሮስ አረጋይ (ዶ/ር)፣ ከየመድረኩ የሚነሱ የሕብረተሰቡ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ ለችግሮች ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
የፍጆታ አቅርቦትን ለማሟላትና የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና ገበያን ለማረጋጋት ከባለሃብቶች፣ ባንኮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት የምግብ እና የምግብ ነክ ግብዓቶች ወደ ክልሉ እየገቡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመቐለ ከተማ አስተዳደር የተጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም አካባቢዎች ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሰላም እንዲጸና እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲጠናከሩ የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: